ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣው እራሱን መስዋዕት አድርጎ በመስጠት የሰው ልጆች ሁሉ ከተበላሸ ህይወታችን አምልጠን ከእግዚአብሄር ጋር እንደገና እንድንገናኝ ነው፡፡ ይህ ዕቅድ በሰው ልጅ ታሪክ ጅማሬ ላይ ይፋ ተደረገ፡፡ ይህም፤ ወደፊት የኢየሱስ መስዋዕት በሚቀርብበት፤ በሞርያም ተራራ በአብርሃም መስዋዕት ምልክትነት በእግዚአብሄር ተፈረመ፡፡ በግብጽ ምድርም የአይሁዶች የፋሲካ መስዋዕት ኢየሱስ ለሚሰዋበት ቀንና ዓመት ምልክት ሆነ፡፡
የኢየሱስ ክርስቶስ መስዋዕት ለምን አስፈለገ? ይህ ጥያቄ በጣም ተገቢ ነው፡፡ በመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲህ የሚሉ ሁለት ህጎች በግልጽ ተቀምጠዋል፤
የሃጢያት ደመዋዝ ሞት ነው . . . (ሮሜ ፮፡፪፫)
የፍጥረት ሕይወት በደሙ ውስጥ ነውና፤ ደሙም ከሕይወቱ የተነሳ ያስተሰርያልና ደም በመሰውያው ላይ ለነፍሳችሁ ማስተሰርያ ይሆን ዘንድ እኔ ለእናንተ ሰጠሁት። (ኦሪት ዘሌዋውያን ፲፯፤፲፩)
“ሞት” ቃል በቃል ሲተረጎም “መለየት” ማለት ነው፡፡ ነፍሳችን ከስጋችን ስትለይ በስጋ እንሞታለን፡፡ እንዲሁም እኛ አሁን በመንፈስ ከእግዚአብሄር ተለይተናል፡፡ ይህ እውነት ነው፤ ምክንያቱም እግዚአብሄር ቅዱስ፤ማለትም ሃጢያት የሌለው፤ ሲሆን እኛ ግን ከመጀመርያ ፍጥረታችን ተለውጠን ተበላሽተናል፤ ስለዚህም ሃጢአትን እንሰራለን፡፡
ይህም በሁለት ተራሮች ሊመሰል ይችላል፤ እግዚአብሄር በአንዱ ጫፍ ላይ ሆኖ መጨረሻ በሌለው ገደል ከኛ ተለይቶ በማዶ አለ፡፡ ከዋናው ዛፍ ተቆርጦ የተለየ ቅርንጫፍ እንደሚሞት ሁሉ፤ እኛም እራሳችንን ከእግዚአብሄር ቆርጠን ስለለየን በመንፈስ ሙት ሆነናል፡፡

ገደል ሁለት ተራሮችን እንደሚለይ እኛም ከሃጢያታችን የተነሳ ከእግዚአብሄር ተለይተናል
ይህ መለያየት ጸጸትና ፍርሃትን ይፈጥራል፡፡ ሰለዚህ ካለንበት የሞት ህይወት ወደ እግዚአብሄር የሚያሻግረንን ድልድይ ለመገንባት እንሞክራለን፡፡ ይህንንም በተለያየ መንገድ እናደርገዋለን፤ ወደ ቤተክርስቲያን በመሄድ፤ ሃይማኖተኛ በመሆን፤ ጥሩ ሰው በመሆን፤ ለድሃ በመመጽወት፤ እራሳችንን በተለያየ መንገድ ለማረጋጋት በመሞከር፤ ለሌሎች ረዳት ለመሆን በመሞከር፤ አብልጠን በመጸለይ፤ ወዘተ፡፡ በተለይም ማንኛዉም አይነት የኦርቶዶክስ፤ የካቶሊክ፤ ወይም የጴንጤ ሃይማኖት ባህላቸው ውስጥ የተለማመዱ ማህበረሰቦች ይበልጡን ሃይማኖታዊ ሥራ በመስራት እንድናስደስተው እግዚአብሄር ይፈልጋል ብለው ያምናሉ፡፡ በስራችን የእግዚአብሄርን ፍቅር ማግኘት መፈለግ ግን በጣም አስቸጋሪ፤ የተወሳሰበና አደገኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም በሚቀጥለው ምስል ለመግለጽ ተሞክሯል፤

መልካም ምግባር ጥሩ ነው፤ ነገር ግን ድልድይ ሆኖ ክእግዚአብሄር ዘንድ አያደርሰንም
ልፋታችን፣ ሃይማኖታዊ ትጋታችንና ምግባራችን ስህተት ባይሆኑም ችግሩ በቂ አይደሉም፡፡ ምክንያቱም ለሃጢያታችን ደሞዝ ወይም ክፍያው “ሞት” ነውና፡፡ ስለዚህም በመልካም ስራችን የመጽደቅ ሙከራችን እስክ መሃል ድረስ ወስዶ ነገር ግን ፈጽሞ እንደማያሻግር ድልድይ ነው፡፡ ይህም ነቀርሳን ጎመን በመብላት ለማዳን እንደመሞከር ነው፡፡ ጎመን መብላት መጥፎ አይደለም፤ እንዲያውም ጥሩ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ነቀርሳን ለማዳን አይጠቅምም፡፡ ለነቀርሳ የተለየ ህክምና ያስፈልጋል፡፡
ይህ ህግ ደስ አይልም ፤ እንደውም ልንሰማው ስለማንፈልግ ያስረሱናል ብለን ተስፋ በማድረግ ህይወታችንን በተለያዩ ምግባሮች እናጨናንቀዋለን፡፡ መጽሃፍ ቅዱስ ግን ይህን የሃጥያትና ሞት ህግ እጅግ አድርጎ በተደጋጋሚ በማንሳት ቀላልና ፍቱን ወደሆነው መፍትሄ ትኩረታችንን ለመሳብ ይሞክራል።
የሃጢያት ደመወዝ ሞት ነው፤ . . . . ግን . . . ሮሜ ፮፡፪፫
“ግን” የምትለው ትንሽ ቃል የመልዕክቱ አቅጣጫ ሊቀየር እንደሆነ ታመለክታለች፤ ይህም ፈውስ ወደሆነው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የምስራች ታመላክተናለች፡፡ የእግዚአብሄርንም ፍቅርና መልካምነት ታሳየናለች፤
የሃጢያት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሄር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው። (ሮሜ ፮፡፪፫)
የወንጌሉ የምስራች የሚነግረን በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት የቀረበው መስወዕት እኛን ከእግዚአብሄር ለለየን ገደል ሙሉና አስተማማኝ ድልድይ ሆኖ እንደሚያገናኘን ነው፡፡ ይህም ዕውነት እንደሆነ የምናውቀው ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞተ ከሶስት ቀናት ቡኋላ በአካል ህያው ሆኖ ስለተነሳ ነው፡፡ አብዛኞቻችን ስለመነሳቱ ማረጋገጫ እንዳለ አናውቅም፡፡ ነገር ግን በዚህ በአንድ ዩኒቨርሲቲ ብዙ ህዝብ በተሰበሰበበት ባደረግኩት ንግግር ላይ ማየት እንደሚቻለው እጅግ አሳማኝ የሆነ ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ መስዋዕትነት በትንቢታዊ ምሳሌ በአብርሃም መስዋዕት በሞርያም ተራራ እና በአይሁዳውያን የፋሲካ መስዋዕት በግብጽ ተከናውኗል፡፡ እነዚህ ክስተቶችህ የተከናወኑት ፈውሱን ወደምናገኝበት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያመላክቱን ነው።
ኢየሱስ ክርስቶስ ያለ ሃጢያት የኖረ ሰው ነው፡፡ ስለዚህ በሰውም በእግዚአብሄርም ፊት መቅረብ ስለሚችል በሁለቱ መሃከል ዕርቅን መፍጠር ይችላል፡፡ እርሱ ከታች በምስል ለመግለጽ እንደተሞከረው የሕይወት ድልድይ ነው፡፡

ኢየሱስ በእግዚአብሄርና በሰው ልጅ መሃከል ያለውን ገደል የሚያገናኝ ድልድይ ነው
የኢየሱስ መስዋዕት ለኛ እንደተሰጠን ልብ በሉ። እንደ “ስጦታ” ነው የቀረበልን። እስኪ ስለስጦታዎች አስቡ። ስጦታው ምንም ይሁን ምን፤ እውነት ስጦታ ከሆነ ምንም ያልሰራችሁበት ወይም በትጋት የሚገኝ አይደለም። በሥራችሁ ካገኛችሁት ስጦታ መሆኑ ይቀርና ደሞዝ ወይም የብድር ክፍያ ይሆናል። እንደዚሁም የኢየሱስ ክርስቶስ መስዋዕት በሥራችሁ ልታገኙት አትችሉም። እንዲሁ በነጻ ተሰጥቷችሗል። ሚስጥሩ የዚህን ያህል ቀላል ነው።
ታድያ ስጦታው ምንድነው? “ዘለአለማዊ ሕይወት” ነው። ይህ ማለት በእኔና እናንተ ላይ ሞት ያመጣብን ሃጢያት ተሰረዘ ወይም ተፋቀ ማለት ነው። የኢየሱስ የሕይወት መስዋዕት ድልድይ ከእግዚአብሄር ጋር እንደገና እንድንገናኝና ለዘላለም የሚዘልቅ ሕይወት እንድንቀበል አስቻለን። እግዚአብሄር እኔንና እናንተን የዚህን ያህል ይወደናል። የወንጌሉም የምስራች መልዕክት የዚህን ያህል ኃይል አለው።
ስለዚህ እኔና እናንተ እንዴት ነው ይህን የሕይወት ድልድይ “የምንሻገረው”? አሁንም ስለስጦታ አስቡ። አንድ ሰው ስጦታ ሊሰጣችሁ ቢወድ እናንተ ልትቀበሉት ያስፈልጋል። ሁልጊዜ ስጦታ ሲለገስላችሁ ሁለት አማራጮች አሏችሁ። ወይ ስጦታውን አልፈልግም ብላችሁ አትቀበሉትም ወይ ደግም እፈልገዋለሁ ብላችሁ አመስግናችሁ ትቀበሉታላችሁ። በኢየሱስ ክርስቶስ መስዋዕትነት የተሰጠንን ውድ ስጦታም ልንቀበለው ያስፈልጋል። በሃሳባችን ብቻ ተቀብለነው ወይ ደግሞ አጥንተነውና ተረድተነው ዝም በማለት አይሆንም። ይልቁንም ከታች ባለው ምስል ለመግለጽ እንደተሞከረው ፊታችንን አዙረን ለኛ በተገነባልን ድልድይ ወደ እግዚአብሄር “ተራምደን” በመቅረብ እርሱ የዘረጋልንን የከበረ ስጦታውን ኢየሱስ ክረስቶስን መቀበል አለብን።

ኢየሱስ በእግዚአብሄርና በሰው ልጅ መሃከል ያለውን ገደል የሚያገናኝ ድልድይ ነው
ታድያ ይህን የከበረ የእግዚአብሄር ስጦታ እንዴት ነው የምንቀበለው? ስለዚህ ነገር መጽሓፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፤የጌታን ሥም የሚጠራ ሁሉ ይድናል ሮሜ ፲፡፲፪
ልብ በሉ፤ ይህ ቃልኪዳን የተሰጠው “ለሰው ልጅ ሁሉ” ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል ነስቶ ከመቃብር ስለተነሳ ህያው ነው፤ ይህም ብቻ ሳይሆን አሁንም “ጌታ” ነው። ስለዚህ፤ ስሙን ብትጠሩት ይሰማችኋል፤ እግዚአብሄርም ይህን የከበረ ስጦታዉን ይሰጣችኋል። ስሙን ጠርታችሁ አነጋግሩት፤ ጠይቁትም። ይሄ ጥንቆላ ወይም ምትሃት አይደለም። የቃላት ምርጫም ጉዳይ አይደለም። ይልቁን እንደ አብርሃም የለመንነውንና የከበረውን ስጦታ እንደሚሰጠን ማመናችን ነው ወሳኙ። ካመንነው ሰምቶ ይመልስልናል። የወንጌሉ የምስራች ሲያዩት ቀላል ነገር ነው፤ ነገር ግን እጅግ ትልቅ ኃይል ያለው ነው። በዚህ መልዕክት ልብህ/ልብሽ ከተነካና ይህንን ለአንተ/ለአንቺ በግል የሞተልህን/የሞተልሽን ጌታ ኢየሱስን መቀበል ብትፈልግ/ብትፈልጊ ከታች ያለውን ጸሎት ከልብህ/ከልብሽ ጸልይ/ጸልዪ።
ውዴ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፤ ከሃጢያቴ የተነሳ ከአምላኬ ከእግዚአብሄር ተለይቻለሁ። እጅግ ተግቼ ብሞክርና በበኩሌ የሚቻለኝን ብዙ ነገር ባደርግ እንኳን በእኔ ጥረትና መስዋዕትነት ይህንን የለየንን ገደል ሊያገናኝ የሚችል ድልደይ በመገንባት ከአምላኬ ከእግዚሃብሄር ጋር መገናኘት አልችልም። ነገር ግን ኢየሱስ ሆይ በደምህ የከፈልክልኝ መስወዕት የኔን ሃጢያት ለማጠብ ብቁ እንደሆነ ገብቶኛል። መስዋዕት ሆነህ ከሞትክልኝ ቡኋላም ሞትን ድል ነስተህ እንደተነሳህ፤ መስዋዕትህም ሃጢያቴን አጥቦ እግዚሃብሄር ፊት ንጹህ አድርጎ ሊያቀርበኝ በቂ እንደሆነ አምኛለሁ። ስለዚህ እባክህን በደምህ ሃጢያቴን እጠብና ዘለአለማዊ ሕይወት እንዲኖረኝ ድልድይ ሆነህ ከአምላኬ ከእግዚአብሄር ጋር አገናኘኝ። ከአሁን ቡኋላ ለሃጢያት ባርያ ሆኜ መኖር ስለማልፈልግ እባክህን ከሃጢያት ነጻ አዉጣኝ። ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ፤ የለመንኩህን ሁሉ ስላደረግክልኝ እጅግ አድርጌ አመሰግንሃለሁ። ከአሁን ጀምሮ ጌታዬና መድሃኒቴ አድርጌ በሕይወቴ ላይ ሾሜሃለሁ፤ እንድከተልህም እባክህን አስችለኝ፤ ምራኝ፤ መንገዴንም አሳየኝ።
አሜን
መጽሐፍ ቅዱስ በተሰሎንቄ ፭፡፲፯ እንደሚነግረን “ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው አልፏል፤ ሁሉም አዲስ ሆኗል”። ስለዚህ ከላይ ያለውን ጸሎት ጸልያችሁ ጌታ ኢየሱስን ከተቀበላችሁ፣ ሕይወታችሁ እንደነበረው አይሆንም፤ ይልቁንም ከታችህ ባለው ምስል ለመግለጽ እንደተሞከረው ሕይወታችሁ ተቀይሮ እጅግ የሚጣፍጥና የሚያረካ ይሆናል። ሃጢያት ተስፋ መቁረጥና ዘላዓለማዊ ሞት ካለበት ከሰይጣን ቤት ወጥታችሁ ጽድቅና ቅድስና፤ ተስፋ፤ሰላምና ፍቅር እንዲሁም ዘላዓለማዊ ሕይወት ወዳለበት ወደ እግዚአብሄር ቤት ተሻግራችኋል።
ከዚህ ቡኋላ አዲሱን ሕይወታችሁን በጥንቃቄ ኑሩ። መጽሐፍ ቅዱስን አጥኑት፤ ተግታችሁም ጸልዩ። ጥሩ ቤተክርስቲያን ፈልጋችሁም ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ሕብረት በማድረግ በእምነታችሁ ለማደግ የሚቻላችሁን ሁሉ አድርጉ። እግዚአብሄርም በመንፈሱ ይረዳችኋል። ተጨማሪ መረጃ ወይም እገዛ ካስፈለጋችሁ ከታች ባለው ኢሜይል አድራሻ ጻፉልን፤[email protected]